Acts 15

የኢየሩሳሌም ጉባኤ

1አንዳንድ ሰዎችም ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው፣ “በሙሴ ሥርዐት መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” በማለት ወንድሞችን ማስተማር ጀመሩ። 2ይህም ጳውሎስንና በርናባስን ከእነርሱ ጋር ወደ ከረረ ጠብና ክርክር ውስጥ ከተታቸው። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ ከሌሎች አንዳንድ ምእመናን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ስለዚሁ ጕዳይ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን እንዲጠይቁ ተወሰነ። 3ቤተ ክርስቲያኒቱም እግረ መንገዳቸውን በፊንቄና በሰማርያ በኩል እንዲያልፉ ላከቻቸው፤ እነርሱም በእነዚህ ቦታዎች ለነበሩት የአሕዛብን መመለስና ማመን ነገሯቸው፤ ወንድሞችም ሁሉ በዚህ እጅግ ደስ አላቸው። 4ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት እንዲሁም ሽማግሌዎች ተቀበሏቸው፤ የተላኩትም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሠራውን ሁሉ ነገሯቸው።

5ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው በመቆም፣ “አሕዛብ እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው” አሉ።

6ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጕዳይ ለማጤን ተሰበሰቡ። 7ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ። 8ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤ 9ልባቸውንም በእምነት በማንጻት፣ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። 10እንግዲህ፣ አባቶቻችንም እኛም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? 11እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።”

12ጉባኤውም በሙሉ ዝም ብሎ፣ በርናባስና ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት በአሕዛብ መካከል ስላደረጋቸው ታምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩ ያዳምጣቸው ነበር። 13እነርሱም ተናግረው ሲጨርሱ፣ ያዕቆብ ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ስሙኝ፤ 14እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን
እርሱም ጴጥሮስ ነው።
አስረድቶናል።
15እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያቱም ቃል ከዚህ ጋር ይስማማል፤

16“ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤
የፈረሰውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ።
ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤
እንደ ገናም እሠራዋለሁ፤
17ይኸውም የቀሩት ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉ፣
ስሜን የተሸከሙ አሕዛብም እንዲሹኝ ነው፤
እነዚህን ያደረገ ጌታ እንዲህ ይላል፤’
18እነርሱም ከጥንት ጀምሮ የታወቁ ናቸው።
አንዳንድ ቅጆች …ለጌታ ከጥንት ጀምሮ የታወቀው የራሱ ሥራ ነው ይላሉ።

19“ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን አሕዛብ እንዳናስጨንቃቸው ይህ የእኔ ብያኔ ነው። 20ይልቁን በጣዖት ከረከሰ ነገር፣ ከዝሙት ርኩሰት፣ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ ከመብላትና ደም ከመመገብ እንዲርቁ ልንጽፍላቸው ይገባል፤ 21የሙሴ ሕግማ ከጥንት ጀምሮ በየሰንበቱ በምኵራብ ሲነበብና በየከተማው ሲሰበክ ኖሯልና።”

ላመኑት አሕዛብ ከጉባኤው የተላከ ደብዳቤ

22በዚህ ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ቤተ ክርስቲያን ጋር ሆነው ከመካከላቸው አንዳንድ ሰዎችን መርጠው፣ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ከወንድሞችም መካከል ዋነኛ የነበሩትን በርስያን የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ፤ 23በእነርሱም እጅ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ላኩ፤

ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፣

ከአሕዛብ ወገን አምነው በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ለሚገኙ ወንድሞች፤

ሰላምታችን ይድረሳችሁ።

24አንዳንድ ሰዎች ያለ እኛ ፈቃድ ከእኛ ዘንድ ወጥተው በንግግራቸው ልባችሁን እንዳወኩና እንዳናወጧችሁ ሰምተናል። 25ስለዚህ ጥቂት ሰዎች መርጠን ከተወዳጆቹ ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ ሁላችንም ተስማምተናል፤ 26በርናባስና ጳውሎስም ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው። 27ስለዚህ እኛ የጻፍነውን በቃል እንዲያረጋግጡላችሁ፣ እነሆ፤ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። 28ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም፦ 29ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከዝሙት ርኩሰት እንድትርቁ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ነገሮች ብትርቁ ለእናንተ መልካም ነው።

ደኅና ሁኑ።

30የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ በዚያም የምእመናኑን ጉባኤ በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው። 31ሕዝቡም ካነበቡት በኋላ አበረታታች በሆነው ቃሉ ደስ ተሰኙ። 32ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለ ነበሩ፣ ወንድሞችን ብዙ ንግግር በማድረግ መከሯቸው፤ አበረቷቸውም። 33በዚያም ጥቂት ጊዜ ከቈዩ በኋላ፣ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ላኳቸው ሰዎች ተመለሱ። 34ሲላስ ግን እዚያው ለመቅረት ወሰነ።
አንዳንድ ቅጆች ይህ ቁጥር የላቸውም።
35ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው የጌታን ቃል እያስተማሩና እየሰበኩ በአንጾኪያ ተቀመጡ።

ጳውሎስና በርናባስ በዐሳብ ተለያዩ

36ጳውሎስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በርናባስን፣ “ተነሣና የጌታን ቃል ወደ ሰበክንባቸው ከተሞች ሁሉ እንሂድ፤ በዚያ ያሉ ወንድሞችም በምን ሁኔታ እንዳሉ ለማወቅ እንጐብኛቸው” አለው። 37በርናባስም ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ አብሯቸው እንዲሄድ ፈለገ፤ 38ጳውሎስ ግን እርሱን ይዞ ለመሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም፣ ቀደም ሲል ማርቆስ ከእነርሱ ተለይቶ በጵንፍልያ ስለ ቀረ እና ወደ ሥራ አብሯቸው ስላልሄደ ነበር። 39እንዲህ የከረረ አለመግባባት በመካከላቸው ስለ ተፈጠረ እርስ በርስ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለጌታ ጸጋ ዐደራ ከሰጡት በኋላ ተለይቷቸው ሄደ፤ 41አብያተ ክርስቲያናትንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል ዐለፈ።

Copyright information for AmhNASV